የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጥምረት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጥምረት በዛሬው ዕለት ይፋ ተደርጓል።
ጥምረቱን የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጭ ኤጀንሲዎች አሰሪ ማህበር፣ የዓለም አቀፍ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አሠሪ ማህበር እና ህብረት ኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አሠሪ ማህበር በጋራ መስርተውታል።
“አንድነት ለዜጎች ደህንነት!” በሚል መሪ ቃል እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በጥምረቱ ዙሪያ በአዲስ አበባ ምክክር አድርጓል።
በዚህ ወቅትም የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ዜጎችን ይበልጥ ለማገልገል መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ መንግስት የጣለውን አደራና ዜጎች ያሳደሩትን እምነት በብቃት መወጣት እንደሚገባው ገልጸዋል።
ለዚህም የኤጀንሲዎች በማህበር መደራጀት ብሎም የፌዴሬሽን ጥምረት መፈጠሩ ሙሉ አቅም እንደሚሆን ይታመናል ነው ያሉት።
ጥምረቱ በተበሰረበት መርህ በአባላቱ ልቦና ውስጥ ሊቀመጥና የተግባር አቅም ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።