በትግራይ ክልል በሰሜን እዝ ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ተያይዞ 349 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ሲወጣ 124ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ. ም በትግራይ ክልል በሰሜን እዝ ላይ ከተፈፀመው ጥቃት ጋር ተያይዞ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግና የፌደራል ፖሊስ የደረሱበትን የምርመራ ውጤት ይፋ አድርገዋል።
መግለጫውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሙስናና የተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ እና የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራልና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም መንግስቴ በጋራ ሰጥተዋል።
በዚህም በሀገር ክህደት ወንጀል፣ በሀገር ሉዋላዊነት ላይ በተቃጣ ጥቃት እና በሽብር ወንጀሎች የተጠረጠሩ 349 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሲሆን 124ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ 680 የሰው እና የሰነድ ምስክርነት የቀረበባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በምርመራው ግኝት ወደ ትግራይ ክልል ሸሽቶ የሄደው ቡድን ላቀዳቸው ወንጀሎች ማስፈፀሚያ በቀዳሚነት የዘመቻ ዘርፍ አቋቁሞ በመቀጠልም ዘርፉን ወደ ትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ በማሳደግ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም አደረጃጀቶቹ የተለያዩ ሰዎችን በመመልመል በበጀት በሰው ኃይል በስልጠና እንዲሁም በመሳሪያ አቅርቦት ድጋፎችን በማድረግ ለጦርነት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ነው የተጠቀሰው።
በዚህም በየዓመቱ 5 ሺህ ሚሊሻ ሲያሰለጥን የነበረው ክልሉ በ2011 ከ47 ሺህ በላይ፣ በ2012 ከ37 ሺህ በላይ ሚሊሻዎችን ማሰልጠኑ በመግለጫው ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ከ5 ሺህ በላይ ልዩ ኃይል ሲያሰለጥን እንደነበርም ተነስቷል፡፡
ኢፈርት፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል፣ መስህቦ፣ ሱር ኮንስትራክሽን እና ሌሎች ድርጅቶች ምሽግ ሲቆፍሩና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የህግ ማስከበር ስራው ከተጀመረ በኋላ መንገድ ቆረጣ ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው ነው ያስረዱት፡፡
በመጨረሻም የጥፋት ኃይሉ ጥቅምት 14 ባደረገው ስብሰባ ለሦስት ወራት የሚሆን የነዳጅ፣ የቀለብ እና ሙሉ የጦር ዝግጅት መፈጸሙንና ወደትገበራ ለመግባት መወሰኑንም የምርመራው ግኝት አረጋግጧል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!