ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን ቀን እንዲያሳውቅ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ-አደር እና የአከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ÷ ተማሪዎች እና ወላጆች የ12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበትን ቀን እየጠበቁ በመሆኑ ፈተናው የሚሰጥበት የተቆረጠ ቀን ለሕዝቡ ሊነገር ይገባል ሲል አሳሰበ።
ኮሚቴው ማሳሰቢያውን የሰጠው የትምህርት ሚኒስቴርን የ2013 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የአርብቶ-አደር እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው በዚሁ ግምገማም ትምህርት ሚኒስቴር ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢወይዘሮ አልማዝ መሰለ÷ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክኒያት በ2012 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና መውሰድ የነበረባቸው ተማሪዎች እስካሁን ፈተናውን አለመውሰዳቸው በተማሪዎች እና በወላጆች ላይ የሥነ-ልቦና ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡
ጫናው በተያዘው ዓመትም እንዳይቀጥል ፈተናው የሚሰጥበት ቀን ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አልማዝ አያይዘውም በመላ ሀገሪቱ 30 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ስላልተመለሱ÷ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን ያማከለ ሥራ መሥራት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
የ8ኛ ክፍል ፈተናን በባለቤትነት የሚመሩት ክልሎች ቢሆኑም የ8ኛ ክፍል ፈተናን አርመው ያልጨረሱትን እና ውጤት ያላሳወቁትን ክልሎች ትምህርት ሚኒስቴር ሊደግፋቸው እንደሚገባ ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡
በአርብቶ-አደር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች በምገባ ፕሮግራም ላልተካተቱት ተማሪዎች እስከ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የምገባ ፕሮግራም እንደሚጀመር መታቀዱ ጥሩ ቢሆንም ኮቪድ እንደገባ ለምገባ ፕሮግራም ዕቅድ ቢዘጋጅ ኖሮ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ የራሱን አስተዋጽዖ ያደርግ ነበር ብለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው÷ ብዙ ቁጥር ያለው ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ፈተና በየጊዜው እየተሰረቀ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ዲጅታላይዝ ለማድረግ ከ400 ሺህ በላይ ታብሌቶች በግዢ ወደ ሀገር እንደገቡ ተፈታኝ ተማሪዎችን በማለማመድ ፈተናውን ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አይይዘው መግለጻቸውን ከህዝበብ ተቀካዮች ምክር ቤት ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!