ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች 80 በመቶ ለሚሆነው ድጋፉ ተደራሽ ሆኗል – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እስካሁን ድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች 80 በመቶ ለሚሆነው ድጋፉን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
መንግስት በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍን ማዳረስ ቁልፍ ተግባሩ አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል በመገኘት በክልሉ እየተከናወነ ስላለው ሰብዓዊ ድጋፍና የኤርትራ ስደተኞች በሚመለከት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከጉብኝታቸው በኋላ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ጉዳዩን በሚመለከት ውይይት አድርገዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በወቅቱ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ማዳረስ ቁልፍ አጀንዳው አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረው እስካሁን ባለው ሂደትም በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች መካከል 80 በመቶ ለሚሆነው ተደራሽ መደረጉን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ድጋፉ በዋናነት የተመጣጠነ ምግብ፣ ውሃ እንዲሁም የጤና ግብዓቶችን ያካተተ መሆኑን በመግለጽ።
በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በስጋት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የነበሩ የኤርትራ ስደተኞችን ወደ መጠለያ ጣቢያ የመመለስ ስራ መከናወኑንም አቶ ደመቀ ጨምረው ገልጸዋል።
መንግስት ያዋቀረው ቡድን ወደ ስፍራው በማቅናት ስደተኞችን የማረጋጋት ስራ ማከናውኑንም ገልጸዋው፤ “በአሁኑ ወቅት ስደተኞቹ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በበኩላቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በበዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ በአብነት የምትጠቀስ አገር መሆኗን ገልጸው፤ “የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለው” ብለዋል።
ወደ ኢትዮጵያ የመጡትም መንግስት ስደተኞችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚለከት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን