ሩሲያ እና ቱርክ በሊቢያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እና የቱርኩ አቻቸው ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን በሊቢያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቀረቡ።
ሁለቱ መሪዎች በሊቢያ ያለውን ግጭት በዘላቂነት መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ ተቀናቃኝ ሃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ልዩነታቸውን በውይይት መፍታት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የመሪዎቹ ጥሪ የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄኮ ማስ በሊቢያ የሚስተዋለው ቀውስ ወደ አላስፈላጊ የእርስ በርስ ግጭት እንዳያመራ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ የቀረበ ነው ተብሏል።
ቱርክ ሩሲያ የጄኔራል ሃፍታር ከሊፋን ጦር ታግዛለች በሚል ትወነጅላለች፤ ሞስኮ በበኩሏ ውንጀላውን ታስተባብላለች።
በተመሳሳይ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ከጄኔራል ከሊፋ ሃፍታር ጋር በሀገሪቱ የተኩስ አቁም ማድረግ በሚቻልበት አግባብ ዙሪያ በሮም መምከራቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኮንቴ በመንግስታትቱ ድርጅት ከሚደገፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ አል ሲራጅ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ሳይሳካ መቅረቱ ተነግሯል።
በሊቢያ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የትሪፓሊ አስተዳደር እና መቀመጫውን በምስራቅ ሊቢያ ያደረገው የጄኔራል ከሊፋ ሃፍታር ጦር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።
በጄኔራል ሀፍታር የሚመራው ጦር ሰሞኑን ከትሪፖሊ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውን የወደብ ከተማ ሲርጥን ተቆጣጥሯል።
በአሁኑ ወቅትም በሲርጥ እና ሚስራታ ከተሞች አካባቢ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑም በዘገባው ተመላክቷል።
የሊቢያ የቀድሞ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከሞቱበት ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ሃገሪቱ በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ትገኛለች።
ከዚያን ጊዜ ወዲህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲሞቱ ሚሊየኖች መፈናቀላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ምንጭ ፦ ቢቢሲ