Fana: At a Speed of Life!

የመልካቁንጥሬ መካነቅርስን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊውን መረጃ የያዘ ሰነድ ተልኳል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የመልካቁንጥሬ መካነቅርስን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ አስፈላጊውን መረጃ የያዘ ሰነድ መላኩን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች የሚገኙ ቅርሶች ያሉበትን ሁኔታ፣ የጥበቃና የእንክብካቤ ሥራውን በተመለከተ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች እያስጎበኘ ነው።

ከተጎበኙ ቅርሶች መካከል በኦሮሚያ ክልል አዋሽ መልካ የሚገኘው የመልካቁንጥሬ መካነቅርስ ይገኝበታል።

የመካነቅርሱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ተሰማ እንዳብራሩት፤ ቦታው ላይ ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያዊያንና በውጭ ተመራማሪዎች ጥናት ሲደረግበት ቆይቷል።

በተለይ በ1975 ዓ.ም በተደረገ ቁፋሮ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ “ሆሞኢሬክተስ” የሚባለው የሰው ዘር በአካባቢው ይኖር እንደነበር የጥናት ግኝት ማመላከቱን አስታውሰዋል።

እንደአቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ በሥፍራው ከ2ሺህ በላይ የተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎች የተገኙ ሲሆን የሰው፣ የጉማሬና የእፅዋት ቅሪተአካላትም እንደተገኙ ነው የገለጹት።

በተጨማሪም በቦታው ላይ ዕድሜው 800ሺህ ዓመት የሚገመት የእንስሳትና የሰው እግር ዳና መገኘቱን አስታውሰው፤ መካነቅርሱን በአግባቡ ማስተዋወቅ ከተቻለ ትልቅ ገቢ ማመንጨት እንደሚችል አስረድተዋል።

ቦታው የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ላይ የያዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የዓለም አቀፍ ቅርስ ጥናት ተመራማሪ አቶ ኃይለስላሴ ደስታ ናቸው።

መካነቅርሱ ለጥናትና ምርምር ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዩኔስኮ ከተመዘገበ የሳይንስ ቱሪዝም መዳረሻ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ግርማዬ በበኩላቸው ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ስለቦታው ዝርዝር የሚገልፅ ሰነድ በቅርቡ ለዩኔስኮ መላኩን አስታውቀዋል።

በዩኔስኮ በኩል ሰነዱን በማየት እስከቀጣይ ወር መጨረሻ ድረስ ምላሹን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አቶ አንዷለም፤ እስከዛው ድረስ ባለስልጣኑ ቦታውን ዝግጁ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የመልካቁንጥሬ መካነቅርስ ከአዲስ አበባ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.