Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎቸ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎቸ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ ወደ መቀሌ ያቀኑት በትግራይ ክልል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከርና በሕግ ማስከበሩ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ማጽናናትን ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በመቀሌ ቆይታቸው ከከተማዋ የአገር ሽማግሌዎችና የነዋሪ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙ ነዋሪዎች የሃይማኖት አባቶች ሠላም ለማስመለስና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን የማበረታታት ሃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን በመሆን መልካም ስራዎችን ማገዝ፣ ሕዝቡን ማገልገልና ስለ ሠላም መስበክ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ሕዝቡ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመከባበርና በመተሳሰብ እንዲኖር የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍ ያለ እንደሆነም ነዋሪዎቹ አመለክተዋል፡፡

በሁሉም የእምነት ተቋማት ስነ-ልቦናን የሚያነቃቁ የተለያዩ መድረኮች መዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው ነዋሪዎቹ የጠቆሙት፡፡

የሃይማኖት አባቶቹ በበኩላቸው ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ለወደፊትም ይህ ድርጊት እንዳይደገም ትውልድም ተስፋ እንዳይቆርጥ የማረጋጋት ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።

ወደ መቀሌ የመጡበት ዋናው ዓላማም ከሕዝቡ ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥና ሕዝቡን ለማጽናናት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለሕዝብ ፍቅርና ርህራሄ ማሳየት፣ ስሜቱ የተጎዳንም ስሜቱን መረዳትና ማጽናናት የሃይማኖት አባቶቹ በመቀሌ ቆይታቸው የሚተገብሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና በመቀሌ ከሚገኙ የእምነት ተቋማት አባቶች ጋር እንደሚወያዩም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.