Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ላደረጉ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን በትግራይ፣ በህዳሴ ግድብ፣ በምርጫ እና በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ዙሪያ ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ላደረጉ የአፍሪካ ሃገራት አምባሳደሮች ገለጻ አደረጉ፡፡

አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ሂደት እና አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ለዲፕሎማቶችና ለአምባሳደሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም የቀጣዩ ምርጫ ሂደት አጠቃላይ ዝግጅት አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት አቶ ደመቀ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲዊ እንደሚካሄድ ነው ያስረዱት፡፡

በገለጻው ወቅት የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የቀጠለው የህዳሴ ግድብ ድርድር አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ አስረድተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል 26 ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች መሰማራታቸውን ገልጸው ስራቸውን እንዲሰሩ የሚያስችላቸው አስፈላጊ ጉዳዮች እንደተሟላላቸው ነው ያብራሩት፡፡

ሆኖም አስፈላጊውን ዶክመንት ሳያሟሉ በክልሉ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉ አካላት ጥያቄያቸውን መንግስት እንደማይቀበል ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ክፍያ መጀመሩን የገለጹት አቶ ደመቀ የገበያ እንቅስቃሴውም በሂደት ወደ መደበኛ ሁኔታው እየተመለሰ መሆኑን ነው ለአምባሳደሮቹ  ያስረዱት፡፡

አቶ ደመቀ በየቦታው የተሰራጩ ኤርትራውያን ስደተኞችን ሰብስቦ ወደ ተሻሉ መጠለያዎች ለማዛወር መንግስት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በታቀደው መሰረት እየሄደ መሆኑን ያብራሩት ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ሁለተኛው ዙር ሙሌትም በመጭው ሐምሌ ወር እንደሚከናወንም ነው ያረጋገጡላቸው፡፡

አምባሳደር ወይንሸት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ህግ ማስከበር ላይ በተሰማራችበት ወቅት የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ መግባቱን ለአምባሳደሮቹ አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ችግር ለመፍታት ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሃገራት ባስቀመጧቸው ስምምነቶች መሰረት ለመፍታት መሞከሩን አብራርተዋል፡፡

አምባሳደሯ በሁለቱ ሃገራት መካከል በፈረንጆቹ 1972 የተደረሰውን ስምምነት በማንሳትም የሱዳን ጦር የአካባቢውን ገበሬዎች በማፈናቀል በኃይል የያዘውን አካባቢ እንዲለቅ አሳስበዋል፡፡

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገላቸውን ገለጻ አድንቀው በጉዳዮቹ ዙሪያ የተሻለ መረዳት እንደሚኖራቸውና ከመሪዎቻቸው ጋርም እንደሚነጋገሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.