Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ጠንካራ ሀገር ትሆናለች – አምባሳደር ፍፁም አረጋ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛውም ሀገር ኢትዮጵያ ከህወሓት የጥፋ ቡድን የገጠማትን አይነት ክህደት ቢገጥመው ምላሹ ምን እንደሆነ ይታወቃል አሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ፡፡

አምባሳደሩ ማንኛውም ሀገር በመከላከያ ላይ የሚፈፀምን ጥቃት አይታገስም ሲሉ አብራተዋል፡፡

አምባሳደር ፍፁም አረጋ ከፓን አፍሪካን ቪዥንስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ወቅታዊ እና ቀጣይ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ጠንካራ ሀገር ትሆናለች ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ከሚዲያው ጋር በዙም በነበራቸው ቃለመጠይቅ ኢትዮጵያን በተመለከተ በአንዳንድ ሚዲያዎች የሚወጣው ዘገባ ከእውነት የራቀ፣ የጥላቻ እና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ እንዳለ እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት መሆኑን በማስረዳት መንግስት ከሱዳንና ግብፅ ጋር በጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በርካታ የውይይት መድረኮችን ሲያካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነትና ፍላጎትም አስረድተዋል አምባሳደሩ፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የአለም ስጋት ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት የተለያዩ ስልቶችን ስትጠቀም መቆየቷን አንስተው እንዲህም ሆኖ ከአፍሪካ ግንባ ቀደም የኢኮኖሚ አፈፃፀም እንዳላት ነው ያስረዱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካውን ለማረጋጋት እና ሀገሪቷን ለማሻገር ይቅርታ ቢያደርጉም የህወሓት የተንኮልና የሴራ ቡድን የጥፋ ተልዕኮውን ባለማቆም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን እና መንግስትም ተገዶ በመግባት የህግ ማከበር ስራን ሰርቶ ማጠናቀቁን አምባሳደር ፍፁም አንስተዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያደርግ ቢቆይም ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ግን በመግባባት እንደሚሰራ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያድግም ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡

በትግራይ ከህግ ማስከበር ስራው በፊት 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ህዝብ በሴፍቲኔት ሲደገፍ መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ ቁጥሩ በ9 መቶሺህ በመጨመር ወደ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግስትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድጋፍ የማቅረብ ስራ እየሰራ መሆኑን አብራተዋል፡፡

የህወሓት የጥፋ ቡድን ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ሲሸሽ በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት በማድረሱ እነዚህን የልማት አውታሮች በመጠገን ወደ ስራ የመመለስ ተግባር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የመብራትና የቴሌኮም አገልግሎት በበርካታ የትግራይ ከተሞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማትን ስለተቀበሉ በሀገራቸው ላይ ክህደት ሲፈፀም ዝም ብለው ባላዩ ማለፍ ነበረባቸው ወይ ሲሉም ጠይቀዋል አምባሳደሩ፡፡

ጉዳዩን በይቅርታ እና በሰላም ለመፍታት እና ግጭትን ለማስቀረት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም የህወሓት የጥፋ ቡድን ግን የሀገር ክህደት በመፈፀሙ መንግስት የህግ የበላነትን ለማስከበር ተገዶ ገብቷ ብለዋል፡፡

መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በውጭ ሀገራ በስደት የነበሩትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ለሰላማዊ ትግል በመጋበዝ ወደሀገር ቤት ማስገባቱን እና ለምርጫም ዝግጅት እያደረጉ እንዳለ ገልፀዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ስራ ላይ ለማዋል ማሻሻያዎችን ማድረጉን አምባሳደር ፍፁም አረጋ አንስተዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.