Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ያለውን የህንድ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ያለውን የህንድ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮ ህንድ የቢዝነስ ፎረም በህንድ የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ተካሄዷል፡፡

አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የተሰማሩ በርካታ የህንድ ኩባንያዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ኩባንያዎቹ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የሁለቱ ሃገራት የንግድ ልውውጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር መድረሱን በመጥቀስም፥ የኮቪድ19 ተፅዕኖ ሳይገድባቸው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ምርጫቸው ላደረጉ የህንድ ኩባንያዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የ10 አመት የኢኮኖሚ ልማት እቅድ በማውጣት ከአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን እየሰራች መሆኗንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ፣ ካለው የሰው ሃይል፣ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ማበረታቻዎች፣ ለባለሃብቶች ካለው ዋስትና እና ከዘርፍ ሙስናን የሚጠየፍ ፖሊሲ አንጻር በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንትና ቢዝነስ ዘርፍ መሰማራት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ አውስተዋል፡፡

የህንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ሙራለድሃራን በበኩላቸው በሃገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት አድንቀው ወዳጅነታቸውን በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ አንስተዋል፡፡

ፎረሙ በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና በህንድ የንግድ ምክር ቤት ትብብር የተዘጋጀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፦ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ዩቲዩብ ቻናል፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.