የጎንደር ከተማ አስተዳደር “በተኩስ ደስታችንን እንገልፃለን” የሚሉ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር “በተኩስ እሩምታ ደስታቸውን የሚገልፁ አካላት” ባላቸው ላይ የሕግ የበላይነትን እንደሚያስከብር ገለፀ፡፡
በሕግ ማስከበሩ ሂደት የተገኙ ድሎችን ምክንያት በማድረግ “ደስታቸውን በተኩስ እሩምታ የሚገልጹ አካላት” የነዋሪውን ህዝብ ተረጋግቶ በሰላም መኖር እና የጎብኚዎችን ደህንነት የሚረብሽ ተግባር እየፈፀሙ መሆናቸውን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ከተገኘው ድል ጋር በተያያዘ ያለውን የአሸናፊነት ስሜት በመረዳትና “በተኩስ ደስታን መግለፅ” ይቆማል በሚል በማስጠንቀቂያ ማለፉን አስታውሷል፡፡
ሆኖም ግን ይህ ሕገወጥ ድርጊት፣ የከተማዋን ገፅታ የሚጎዳ፣ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችንና ፍጹም ሰላማዊ ሕዝቦችን የሚረብሽ በመሆኑ የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የፀጥታ ኃይል ከአሁን በኋላ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብር፣ ድርጊቱን በሚፈፅሙ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጿል፡፡
ይህን ሕገወጥ ድርጊት ሽፋን በማድረግም ወንጀል ለመስራት የሚጥሩ አካላት እንደሚኖሩ የከተማ አስተዳደሩ እንደሚገነዘብም ነው የገለፀው፡፡
በመሆኑም ደስታን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለጽ ሲቻል፣ በጥይት ተኩስ እንገልፃለን የሚሉ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ እሰራለሁ ብሏል የከተማ አስተዳደሩ፡፡
ነዋሪውም ይህንን አውቆ በሕገወጥ ተግባራቸው ከተማዋን እየጎዱ ያሉ አካላትን ስርዓት ለማስያዝ መንግሥት በሚያደርገው ህግን የማስከበር ዘመቻ ከጎኑ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!