በአማራ ክልል የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ሰዎች የነጻ ህክምና መስጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ሕጻናትና አዋቂዎች የነፃ ህክምና መስጠት መጀመሩን የጥበበ ግዮን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል፡፡
በሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘበናይ ቢተው እንደተናገሩት ሕክምናው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት ይሰጣል፡፡
ዶክተር ዘበናይ ሕክምናው የጥበበ ግዮን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከፕሮጀክት ሃረር ኢትዮጵያ እና ስማይል ትሬን ከተባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተሩ መረጃ በአማራ ክልል በርካታ ሕጻናትና አዋቂዎች የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር አለባቸው፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምናው የሚሰጥ ቢሆንም በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑ ሁሉንም ማዳረስ አልተቻለም ነው ያሉት፡፡
የሕጻናቱንና የአዋቂዎችን ስቃይ እና የአስታማሚዎችን መጉላላት ለመቀነስ ሕክምናውን በዘመቻ መስጠት ማስፈለጉንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዘመቻ አገልግሎቱን ያላገኙ ሕፃናትና አዋቂዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ቀጣይ ዘመቻ መዘጋጀቱን አብመድ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ዘመቻ ከ80 በላይ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸው ሕፃናትና አዋቂዎች ሕክምና ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!