Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የከተማዋን የ2 ወራት የፅዳት ንቅናቄ አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “አካባቢዬን በማጽዳት ለከተማዬ ጽዳትና ውበት አምባሳደር ነኝ!” በሚል መሪ ቃል የፅዳት ንቅናቄ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክ/ከተማ ተጀመረ።

ንቅናቄው በከተማ ደረጃ የሚካሄድ ሲሆን ለ2 ወራት የሚቆይ ይሆናል።

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በከተማዋ 25ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሚሆኑበትን የጽዳት ዘመቻ በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት ውብ እና ፅዱ አዲስ አበባን ማየት እፈልጋለሁ፣ከተማዬን እወዳታለው የሚል ሁሉ ለፅዳትዋ መትጋት አለበት ብለዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ በመገኘት የጽዳት ዘመቻውን ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከግላችን ጀምረን አካባቢን ማጽዳት ባህል ሆኖ ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የጽዳት ዘመቻው በሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣በትምህርት ቤቶች ፣በጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ በሃይማኖት እና ልዩ ልዩ ተቋማት ሰራተኞችን እና ነዋሪዎችን በማሳተፍ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ከማለዳው 12፡00 ጀምሮ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ታወቂው የኪነጥበብ ባለሙያ አርቲስት ደበበ እሸቱን ጨምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ፣ የጽዳት ሰራተኞች እና ነዋሪዎች ተሳተፊ ሆነዋል፡፡

ፈቲያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.