የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎቻቸው ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ስምንት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ተሽከርካሪ እንዲመጣላቸው ወደ ጥሪ ማዕከል በመደወል እና መንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኙትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪ በማስቆም መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህም ተጠርጣሪዎቹ ከተሳፈሩ በኋላ ወንጀሉን ለመፈፀም የመረጡት ቦታ ላይ ሲደርሱ እዚያዉ ከሚጠብቋቸው ሌሎች ግብራበሮቻቸው ጋር በመተባበር “ከኋላ የምንጭነው ዕቃ አለ ኮፈኑን ክፈትልን” በማለት አሽከርካሪውን እንዲወርድ ካደረጉ በኋላ ጉዳት አድርሰው ተሽከርካሪውን እና የአሽከርካሪውን ሌሎች ንብረቶች ይዘው ሲሰወሩ ቆይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከል የክትትል አባላት ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት መረጃ የማሰባሰብ እና የክትትል ስራ የወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
በሂደቱም ተጠርጣሪዎቹ 8 ተመሳሳይ ወንጀሎችን መፈፀማቸውን በምርመራ ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ተሽከርካሪዎቹን ከወሰዱ በኋላ አካላቸውን በታትነው እንደሚሸጡ ተረጋግጧል፡፡
እስካሁን በተገኘው መረጃም ከተወሰዱት 8 ተሽከርካሪዎች መካከል በፖሊስ ክትትል እና በህብረተሰቡ ትብብር 6ቱ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
እስካሁን በተከናወነው ተግባር 4 የወንጀሉ ዋና ፈፃሚዎች፣ 2 ባለጋራዦች፣ 1 ደላላ እና 1 የተሽከርካሪዎቹን አካል የሚፈታታ በአጠቃላይ 8 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!