በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት በ119 የግጭት አደጋዎች ከ5 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።
87 ግጭቶች ከቀለበት መንገድ ውጭ ባሉ የመንገድ ሐብቶች ላይ ሲደርሱ 32 ግጭቶች ደግሞ በቀለበት መንገድ በሚገኙ የመንገድ ሐብቶች ላይ የደረሱ ናቸው ተብሏል።
በግጭቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የመንገድ ሐብቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በመንገድ ሐብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስም በመንገድ ሐብት ላይ የተመዘገበው የአደጋ ቁጥር ግን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ መቀነሱ ነው የተነገረው።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መንገዶችን በአግባቡ መጠቀምና በጋራ መንከባከብ ይገባዋል መባሉን ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።