በአዲስ አበባ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 396 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ወንጀሎች የጠረጠራቸውን 396 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የክስ መዝገብ የከፈተ ሲሆን፥ ግለሰቦቹ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ፣ የገንዘብ ዝውውር፣ የመሬት ወረራ፣ የመኪና ስርቆት እና ሌሎች ወንጀሎች ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ መሆኑን የኮሚሽኑ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ባለፉት ስድስት ወራት በተሰሩ ስራዎች በጸጥታ አካላት እና በህብረተሰቡ ትብብር 2 ሺህ የተለያዩ ሽጉጦች እና 18 ሺህ 354 የሽጉጥ ጥይት፣ 113 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ እና 8 ሺህ 655 የክላሽ ጥይት፣ 4 ብሬን እና 119 የብሬን ጥይት መያዙን ተናግረዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ብርን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ እና ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች መያዛቸውንም ገልጸዋል።
በዚህም 8 የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ከሃሰተኛ የብር ኖት ማተሚያ መሳሪያ ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ ተወስዶ የነበረ 6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለመሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።