ሙስናን በጊዜ ካላጠፋነው እንደካንሰር ሆኖ ሊያጠፋን ይችላል – ፕሬዚዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ተከብሯል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተገኝተዋል።
በምስረታ በዓል አካባበሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ÷ “ሙስናን በጊዜ ካላጠፋነው እንደካንሰር ሆኖ ሊያጠፋን ይችላል” ሲሉ ገልጸዋል ።
ፕሬዚዳንቷ በጥሬ ገንዘብ እና በአይነት ከሚሰራ ሙስና ይልቅ በዘመድ እና በብሄር የሚሰራ ሙስና በቅን አገልጋዮች ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ቀላል አይደለም ብለዋል።
ሙስናን የመከላከሉ ተግባር ለአንድ ተቋም የሚተው ሃላፊነት አለመሆኑን በመጥቀስም፥ የፍትህ ተቋማት በሙሰኞች ላይ የሚደረገውን የህግ ሂደት ለህዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አንስተዋል፡፡
ይህም ለህብረተሰቡ ማስተማሪያ እንደሚሆንም አውስተዋል።
“ዛሬ ነገ ሳይባል ሙሰኞችን መከላከል ይገባል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ።
የተወሳሰቡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ መሥራት እንደሚገባም በዚህ ወቅት አሳስበዋል፡፡
በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች በባህሪያቸው የተደራጁና የተወሳሰቡ በመሆናቸው የሁሉንም ክትትል ይጠይቃሉም ነው ያሉት።
በተለይም በኃላፊነት ላይ የሚገኙ አመራሮች በሚመሯቸው ተቋማት ለሙስና አጋላጭ የሆኑ አሠራሮችና ሥርዓቶችን ሊያስወግዱ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።
ሠራተኞችም በአቋራጭ መበልጸግን በማስወገድ ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ሃብት በማፍራት እንዲያስመዘግቡም መክረዋል።
ፕሬዚዳንቷ ሙስና በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚካሄደውን የፍርድ ሂደት ለኅብረተሰቡ ግልጽ በማድረግ እንዲማርበት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የሚደረገውን ትግል ሁሉም ካልተቀላቀለ ወንጀሉ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ በተለይም ሙስናን በመከላከል የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
በምስክር ስናፍቅ