ክልሉን ከማናቸውም ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል-አቶ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ክልሉን ከማናቸውም ጥቃት ለመመከት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡
ርዕስ መስተዳድሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ የአማራ ሕዝብ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን መሥራቱን አውስተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰነው ውሳኔ በክልሉ መንግሥት እንደሚደገፍም ነው የገለጹት፡፡
የአማራ ሕዝብና መንግሥት ለመከላከያ ደጀን መሆኑን አሳይቷል፣እያሳየም ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለንም ነው ያሉት።
ክልሉን ከማናቸውም ጥቃት ለመመከት አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ማንሳታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ለአሸባሪው ህወሃት ዋጋውን የሠጠና የደመሰሰ መሆኑን በመግለጽም አሸባሪው እዚህ ግባ የሚባል ተፅዕኖ እንደማያደርስ ተናግረዋል፡፡
የአሸባሪው ትህነግ ዓላማ የተዳከመ የመከላከያ ሠራዊት እንዲፈጠር ማድረግ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ለወራት የዘለቀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በድል የተጠናቀቀ ነውም ብለዋል።
መንግሥት በአሸናፊነት ላይ ሆኖ ያወጀው የተኩስ አቁም መሆኑንም አስታውቀዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን የቻለውን በደል ሁሉ በአማራ ሕዝብ ላይ ፈፅሟል ነው ያሉት።
የአማራ ሕዝብና የጸጥታ ኃይሉ የአሸባሪውን ትህነግ ተስፋፊነት መግታቱንም ነው ያመላከቱት፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሂሳብ የሚያወራርድበት እና ቆሞ የሚጠብቅ ሕዝብ የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ እኛ በማንም ሕዝብ ላይ ሂሳብ አናወራርድም፤ እናወራርዳለን ብለን አልተነሳንም፣ የሚመጣ ካለ ግን ዝግጁ ነን ብለዋል።
ከአሸባሪው ትህነግ የሚመጣውን ጥቃት ለመመከት ብቃትም ችሎታውም አለን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
የአማራ ሕዝብ በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ ወጣቱ፣ ሚሊሻውና ልዩ ኃይሉ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
ክልሉ አሁን ላይ መደበኛ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን።