በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የክምችት መጠን ለማወቅ ጥናት ተጀምሯል – ባለሥልጣኑ
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት የክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ክምችት መጠንን ለማወቅና ለይቶ የበለጠ ለመጠቀም በሚያስችልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂዷል።
በምክክሩ ላይ አማካሪ ኩባንያዎች ወደ ፊት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ ከምርምር ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ጥናት ዳይሬክተር ዶክተር ዘበነ ላቀው እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ ያላት የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት በአግባቡ እየተጠቀመች አይደለም።
ውሃ ይገኝበታል ተብለው የተቆፈሩ ቦታዎችም በቂ ውሃ የማይሰጡበት ሁኔታ መኖሩንም ነው ያነሱት።
እንደ ዶክተር ዘበነ ገለጻ፥ አገሪቷ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም ያልቻለችው በአግባቡ ጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ ባለመሰራቱ ነው።
ችግሩን ለመፍታትም የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ ቃል በገባው መሰረትም በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በሚገኙ በ53 ወረዳዎች የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ክምችት መጠን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን ገልጸዋል።
ጥናቱ የትኛው አካባቢዎች ቅድሚያ ይሰጣቸው የሚለውን መሰረት በማድረግ በድርቅ የተጎዱና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ያረፈባቸው በመለየት የሚካሄድ ነው።
ለዚህም ሦስት አማካሪ ድርጅቶች ተመርጠው ከአንድ ወር በፊት ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው፥ ጥናቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተረጋገጠ የውሃ ሀብት መኖሩን የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በደረቃማ አካባቢዎች ጤና ኬላዎች ተቋቁመው ውሃ ለማግኘት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ዘበነ፥ ጥናቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተው፥ ጥናቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 17 ነጥብ 95 በመቶ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን፥ በአድአ በቾ፣ አላይደጌ ብሌንስ፣ ቴሩ ጭፍራ፣ ቆቦ ጨፋ፣ ቆቦ ጊራ፣ ራያ፣ ቦረና እና ሽንሌ የመሳሰሉ ቦታዎች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
መንግሥት የከርሰ ምድር ውሃን ለመስኖ ልማትና ውሃ አቅርቦት ለማዋል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኢምባሲ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና ውሃ አቅርቦት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ የወንድወሰን አንተነህ በበኩላቸው፥ የእንግሊዝ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግስት ጋር በከርሰ ምድር ውሃ ሃብት መረጃና አቅም ግንባታዎች ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የትምህርት፣ ጤናና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ሥራ ለማስቀል የውሃ አቅርቦት ወሳኝ ነውም ብለዋል።
በዚህና መሰል ስራዎች ላይ የእንግሊዝ መንግሥት 100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ገንዘብ መድቦ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑም አክለዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!