ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሁለት ተርባይኖች ሀይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን መያዝ አስችሏል- ኢ/ር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በሁለት ተርባይኖች ሀይል ለማመንጨት የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን መያዝ ማስቻሉን የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በዚህ ዓመት በርካታ ስራዎች መሰራቱን ያነሱት ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ይህን ተከትሎም አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
ቀጣዩ ስራም ከሁለት እስከ ሶስት ወራት የሁለቱን ተርባይኖች ተከላ በማጠናቀቅ የማመንጨቱን ስራ ወደ ተግባር ማስገባት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የውሃ ሙሌት ትልቅ ውጤት መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ዋነኛው ውጤት ግን ሃይል ማመንጨትና ኤሌክትሪክ ለህዝቡ ማቅረብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ለዚህም ስራውን በማጠናቀቅ የእሱን ብስራቱ በቅርብ ጊዜ ለህዝቡ እናደርሳለን ፤ለእሱም የሚያበቃን በቂ ውሃ ይዘናልም” ነው ያሉት፡፡
ሚኒስትሩሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሃገራት ምንም ያስተጓጎለባቸው ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አንጻርም ሶስቱ ሃገራት እንዴት ብልፅግናን ማስቀጠልና እንዴት ማደግ እንችላለን የሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
አያይዘውም ግድቡ ሰፊ ልማት ማልማት እንደሚስችላቸውና ለጎርፍ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!