የተለያዩ ክልል ልዩ ኃይሎች የሕዳሴ ግድቡን ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ግዳጃቸውን ለመወጣት ቁርጠኞች መሆናቸውን የደቡብ፣ ሲዳማ እና የጋምቤላ ክልል ልዩ ሃይሎች ገለጹ።
ሃገራዊ ጥሪውን ተቀብለው በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ ቀጠና ግዳጅ ለመወጣት ለመጡ የክልሎቹ ልዩ ኃይል አመራርና አባላት የስራ ስምሪትና መመሪያ ተሰጥቷል።
የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ፤ በተወሰደው የሠላም ማረጋጋት እርምጃ በቀጠናው ሠላም መስፈኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ሲፈጠር የነበረውን ሞትና መፈናቀል በማስቆም ታጥቀው ጫካ ገብተው ለነበሩ ታጣቂዎች የሠላም ተሃድሶ ስልጠና መሰጠቱንና ተፈናቃዮችን ወደ የወረዳቸው መመለስ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
የልዩ ኃይል አባላቱ ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደ መተከል በመምጣታቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጠናው የሚገኘው የኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ እንዲወጡም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የደቡብ ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ የልዩ ኃይል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮሚሽነር አለማየሁ ባውዲ የሕዳሴ ግድብ ቀጠና ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተገኘው እድል ያኮራል ብለዋል።
የልዩ ኃይል አባላት በበኩላቸው በቀጠናው ማንኛውም ጸረ ሠላም ኃይል ለመፈጸም የሚያስበውን እኩይ ዓላማ ለመመከት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የሃገር ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህነንትና ሠላም ለማስጠበቅ የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
የተሰጣቸው ግዳጅ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ያካተተ በመሆኑ ኩራት እንደሚሰማቸውና በአሸናፊነት ለመወጣት እንደሚተጉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!