Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሯቸው ዘገባዎች የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካ ፍላጎት ማንጸባሪቂያ ናቸው – ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምሁራን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊና ገለልተኛ ባልሆነ መልኩ የሚሰሯቸው የዜና ዘገባዎች የምዕራቡን ዓለም የፖለቲካ ፍላጎት ማንጸባሪቂያ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን ሚዲያዎቹ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ወታደራዊ ጥቅሞች አንጻር ትርፉን የሚያሰላ የዜና ዘገባ ለሀገሪቱ ምን ውጤት ያመጣል ከሚል ፅንፍ ብቻ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህሩ አቶ አያሌው ደጀን ስመ ጥር መገናኛ ብዙሃን የሀገራትን ሉዓላዊነት እስከመድፈር የሚደርስ የአራተኛ መንግስትነታቸውን ለፖለቲካዊ አላማ የሚጠቀሙበት ሆነዋል ነው ያሉት ።

ለአብነትም ህጻናትን በጦርነት የመሪ ተዋናይነት ሚና ስለሰጣቸው የሽብር ቡድን የሚያወግዝ መረጃን ከመስጠት ዝምታ መምረጣቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ መምህር አቶ አስማማው አዲስ የዜና መረጣቸው እና የሚሰራበት ቅርጽ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን አላማ እና የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት አቋም ጋር የተናበበ እስከሚመስል ድረስ የፖለቲካ መሳሪያ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

የምዕራቡ ዓለም ጣልቃ ገብነት ከአፍጋኒስታን እስከ ሊቢያ ሲዘረጋ ለሀገራቱ ሉዓላዊነት ጉዳይ እንዳልሰጡት አስታውሰው፥ ከሊቢያና የመን ፍርስራሾች ስርም አትራፊ ዜና ፍለጋ አየራቸውን ሲጠቀሙ እንጂ የጋዜጠኝነትን መርህ ሲገልጡ አለመታየታቸውን ያነሳሉ፡፡

አሁን ላይም የቆየ አካሄዳቸው ወደ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት እየዳዳ ይመስላልም ነው ያሉት።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ ሚዲያዎቹ ያደረሱትን ተጽዕኖ በመገምገም መንግስት አማራጭ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን መጠቀም ይጠበቅበታል።

ለዚህም በሀገራት የውስጥ ጉዳይ የመግባት ፍላጎት የሌላቸውና የአዳጊ ሀገራት ጉዳይ የሚገዳቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የምዕራብ ዘመም ሚዲያ ተገዳዳሪ መገናኛ ብዙሃንን በስፋት መጠቀም ይገባልም ነው የሚሉት ።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሚዲያዎችም የእንግሊዝኛ እና አረቢኛ የቋንቋ ተደራሽነታቸውን በማስፋት ሀገርን ከምዕራብ ዘመሙ የጋዜጠኝነት መርህን እንዳሻው ከሚጠቀመው ሚዲያ ጋር የሚገዳደር ዘገባ ማስተላለፍ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሀይለየሱስ መኮንን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.