Fana: At a Speed of Life!

አንዳንድ አካባቢዎች ከሚፈጠሩ መጠነኛ ግጭቶች ውጪ ሞትና መፈናቀልን ማስቀረት ተችሏል- ብ/ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ

አዲስ አበባ ፣ሃምሌ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)አንዳንድ አካባቢዎች ከሚፈጠሩ መጠነኛ ግጭቶች ውጪ ሞትና መፈናቀልን ማስቀረት መቻሉን ብ/ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገለጹ፡፡

በመተከል የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት የተቀመጡለትን ግቦች በሚገባ ማሳካት መቻሉን የኮማንድ ፖስቱ አባል ብ/ጄኔራል አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ጄኔራሉ በመተከል ዞን ለተሰማራው ሁለተኛው ዙር የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ባደረጉት የግዳጅ ቀጣና ገለፃና የስራ መመሪያ ንግግራቸው፥ ኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባ መፈፀሙንና ግዳጁን ለመፈፀምም በርካታ መስዋእትነት መከፈሉን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሰው ሞትና መፈናቀልን ማስቀረት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የህዳሴ ግድብን ቀጠና የሰላም ሁኔታ ማረጋገጥ የኮማንድ ፖስቱ ዋነኛ ተልዕኮዎች መሆናቸውን ጀኔራል መኮንኑ ጠቁመዋል፡፡

ተፈናቃዮችም ወደ ወረዳዎች የተመለሱ ሲሆን፥ አንዳንድ አካባቢዎች ከሚፈጠሩ መጠነኛ ግጭቶች ውጪ ሞትና መፈናቀልን ማስቀረት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ዋና ከተማ የሆነው ግልገል በለስ ከተማ በግጭቱ ወቅት ወደ ህዳሴ ግድብ የሚደረገው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ተስተጓጉሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተፈፀመው ስኬታማ ተልዕኮም ይህንን ሁኔታ መለወጥና ቀጣናውን ሰላማዊ በማድረግ የግድቡ ሁለተኛው ሙሌት በሰላም የተፈፀመበትን ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር አሸናፊ ቴዎድሮስ በበኩላቸው፥ በዚህ ወሳኝ ወቅት የክልሉና የፌደራል መንግስታት ከባድ አደራ ጥለውብናል ያሉ ሲሆን፥ ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ህዝብና ሃገራቸውን ለማኩራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የሰራዊት አባላቱም የሀገራችንን አንድነት በመፈታተን ልማታችንን ለማደናቀፍ የተነሳብንን የአሸባሪው ህወሀት ጁንታ ሴራ ከኢፌዴሪ መከላከያና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን እናመክናለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.