በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ በርካታ ብረታ ብረት ተያዘ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ በርካታ ብረታ ብረት መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አሸባሪው የህዋሓት ጁንታ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስና የሀገር ማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያዩ የኢኮኖሚ አሻጥር መረቦችን ዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱን ፖሊስ በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
ብረታ ብረቶቹ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በ17 መጋዘኖችና በተለያዩ ስፍራዎች ተደብቀው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት ዋጋ እንዳላቸው በመጥቀስም ፖሊስ ከህዝቡ የደረሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰሞኑን ባደረገው ዘመቻ ተይዘዋልም ነው ያሉት፡፡
በዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ተጠርጣሪዎችንም በመያዝ ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አሸባሪው ህወሓት ሀገርን ለማወክ ሊጠቀምባቸው ያዘጋጃቸውን የገንዘብ ምንጮች በመለየት እካአሁን ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ እንዳይንቀሳቀስ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
ጁንታው የሀገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም ከሚያከናውናቸው እኩይ ተግባራት አንዱ በግንባታው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደርና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍጠር ህዝብና መንግስትን ማጋጨት ዋነኛው መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ጁንታው ድልድዮችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን እንሰራለን በሚል በመንግስት ውሳኔ ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸውንና በርካታ የውጭ ምንዛሬ የወጣባቸውን ብረታ ብረትና ሌሎች የልማት ቁሳቁስ በህገ-ወጥ መንገድ በማከማቸት በስራ ላይ እንዳይውሉ ማድረጉ ወንጀል መሆኑንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡
ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ የማጣራትና የፍተሻ ስራ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ተደብቆ የተገኘ ሲሆን፥ ከአሸባሪው የህወሓት ጁንታ ጋር ህብረት ፈጥረው በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላትን በመያዝ ፖሊስ የምርመራ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!