የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተመራ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የልዑካን ቡድን በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኡስማን ዲዮን ከተመራው በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎች ቡድን ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ሽግግርና ቀጠናዊ ትስስር ፕሮጀክት በአዲስ አበባ የሚገነባው የከፍተኛ ትምህርት የጥራት ማረጋገጫ ማዕከል ግንባታ ስለደረሰበት ደረጃ ገለፃ ቀርቧል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ÷ የዓለም ባንክ ቡድን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በተለይም ለምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ለሽግግር እና ለቀጠናዊ ተስስር ፕሮጀክት እያደረገ ስላለው ድጋፍ አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ያረጋገጡ ሲሆን፣ የዓለም ባንክ ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኡስማን ዲዮን በበኩላቸው ÷በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በታቀደላቸው መሰረት እየተመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓለም ባንክ በዘርፉ የሚደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውንም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!