Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከተመድ የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በትግራይ ጉዳይ ላይ ማብራያ የሠጡት ምክትል ጠቅላይ ሚነስትሩ፥ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች የዝናቡን ወቅት እንዲጠቀሙ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም በህወሓት በኩል ባለመተግበሩ እንዳልተሳካ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ሕወሓት መጥፎ ምግባሩን የቀጠለና ለመንግስት በጎ ፈቃድ አክብሮት እንደሌለው ቢገልፅም አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ለተኩስ አቁም ቁርጠኛ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

አቶ ደመቀ ህወሓት በአዲስ አበባ – ጅቡቲ መስመር ላይ ያሉ ሰብአዊ መተላለፊያዎችን ለማስተጓጎል መሞከሩን ጠቅሰው፥ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ተስፋ ለማስቆረጥ የሰሜን ምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ላይ አዲስ ጥቃት ጀምሯል ብለዋል፡፡

ከታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ጉዳዩን ፖለቲካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ማድረግ የድርድር ሂደቱን ከመጎተት ውጭ ጥቅም እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአፍሪካ ህብረት በሚመራው የድርድር ሂደት ለሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች ሰላማዊ መፍትሄዎች ላይ እንዲደርሱ የተባበሩት መንግስታት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

6ኛውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተም ምርጫው ሰላማዊና ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወኑን በመጥቀስ፥ ሂደቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ለመገንባት መንገድ የከፈተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ግጭት ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን በሕገ-ወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ግዛቶች መያዟን አለማውገዙ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ በበኩላቸው፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ሁለገብ የሰብአዊነት የተኩስ አቁም ውሳኔውን በማድነቅ እና በመደገፍ ሌላኛው ወገንም መከተል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለቀጠናው ሰላም ያለውን ፋይዳ ተመድ እንደሚረዳ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.