የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ለመማር ይጠቅማል – ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የህይወት ታሪክና ስራዎች ላይ ያተኮረ መፅሐፍ ተመረቀ።
በደራሲ ዓለምነህ ረጋሳ የተዘጋጀው መፅሐፍ “ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ እና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከ1949 ዓ.ም እስከ … ” የሚል ርዕስ ያለው ነው፡፡
በመፅሐፍ ምረቃው ላይ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት ከማገልገላቸውም በተጨማሪ በሌሎች ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት በአምባሳደርነት በድምሩ ከ30 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በመፅሐፍ ምረቃው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት መፅሐፉ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ለመማር ይጠቅማል ብለዋል፡፡
ብዙ ልምድ ያካበቱና ፈተናዎችን ያለፉ ሰዎች ታሪክ ተከትቦ ቢቀመጥ ለትውልድ መማሪያ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኔትዎርክ ማዕከል የተሰኘ ተቋም በዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መስራችነት መቋቋሙም በመድረኩ ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡
ማዕከሉ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ረገድ ያሉ ጥረቶችን ለመደገፍና ክፍተቶችን ለመሙላት ያለመ መሆኑን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተቋሙ በኢትዮጵያ ያለው ኢንቨስትመንት እንዲጎለብትና ዘላቂ እንዲሆን ይሰራልም ተብሏል፡፡
ዶ/ር ሙላቱ ከዚህ ቀደም ለሀገሪቱ ኢንቨስትመንት መሳካት የሰሩና አሁንም ድጋፍ እያደረጉ ያሉ መሆናቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!