የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ2 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያዳበርነውን አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠልና ጉድለቶችንም ለማረም በጋራ በመሥራት ከድህነትና ኋላቀርነት በመላቀቅ ወደ ሕብረብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንተባበር ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ለማፅናትና የኢትዮጵያን አንድነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ተመራቂዎቹ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ለኢትዮጵያውያን በፍፁም ሥነ ምግባርና ከአድሎነት በራቀ መንገድ እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር በሽር አብዱላሂ ኢትዮጵያ በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን ያሰበችውን ራዕይ ለማሳካት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስክ መደልደላቸውን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ከብልሹ አሠራር ራሳቸውን በማራቅ ለሀገራቸው እድገት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለ13ኛ ጊዜ ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በማስመረቅ ለሀገርና ለክልሉ እድገት የድርሻውን አስተዋጽዖ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በብስራት መለሰ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!