በኮሮና ቫይረስ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ጨመረ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሳምንታዊ አማካይ የሞት መጠን በእጥፍ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለፀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ÷ ወደ ህክምና ተቋማት የሚገቡ የህሙማን ቁጥርም የ 2 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ሳምንታዊ አማካይ የሞት መጠን ደግሞ ከ13 ወደ 36 አድጓል ያሉ ሲሆን÷ በፅኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ የቫይረሱ ስረጭት እየጨመረ ቢሆንም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የሚቀሙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡
በዚህም በአዲስ አበበ 59 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ደግሞ 20 በመቶ ብቻ ናቸው የአፍና አፍንጫ ማስክ የሚጠቀሙት ብለዋል ሚኒስትሯ።
አሁን ቫይረሱ ያለበት ስርጭት 3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ የስርጭት ማዕበል የጀመረ መሆኑን ያመለክታል ያሉት ዶክተር ሊያ ህብረተሰቡ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች በመማር ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ከመጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 2 ሚሊየን 254 ሺህ 270 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ወስደዋል።
ከ 300 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ሁለተኛ ዙር ክትባት መውሰዳቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ ቀሪውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እይተሰራ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ቫይረሱ ካለው የስርጭት አሳሳቢነት በመነሳት ከዚህ ቀደም የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያልወሰዱ እድሜያቸው ከ 35 አመት በላይ የሆኑ ፣በሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ደግሞ እድሜያቸው ከ 55 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ክትባቱ ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው እድሜያቸው ከ 18 አመት በላይ የሆኑ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ሰዎች እንዲሁም በስራቸው ምክንያት ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ክትባቱ ይሰጣቸዋል።
ክትባቱም በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ክልሎች ደግሞ ከነሀሴ 14 ጀምሮ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!