የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ዳግም እንዘምታለን- የቀድሞ ሠራዊት አባላት
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስትን ጥሪ በመቀበል አሸባሪውን የህወሓት ርዝራዥ ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ለመሳተፍ ዳግም እንዘምታለን ሲሉ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት አስታወቁ።
ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡት አስር አለቃ ንጉሴ መንገሻ÷ መንግስት በሆደ ሰፊነት አሸባሪው ህወሀት ከጥፋት ድርጊቱ ተቆጥቦ ወደ ሰላም ይመለሳል ብሎ ቢጠብቅም ሊሳካ አልቻለም ብለዋል።
ምንም እንኳን መንግስት በጥፋት ቡድኑ ላይ እርምጃ አለመውሰዱ የዘገየ ቢሆንም ሀገራዊ ጥሪው ተገቢና የሚደግፉት መሆኑን አስታውቀዋል።
ህወሃት ቀድሞም የውሸት ፕሮፓጋንዳ ያደገበት የትግል ስልቱ በመሆኑ በዚህ ማንም ሊታለል እንደማይገባ የተናገሩት ደግሞ አስር አለቃ አለማየሁ ገሜዴ ናቸው።
ሀገር ስትፈርስ ቁጭ ብሉ የሚያይ የለም የሚሉት አስር አለቃ አለማየሁ የመንግስትን ጥሪ በግንባር ቀደምትነት ተቀብለው ዳግም ለመዝመት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች ለሀገራቸው ክብርና ሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
መቶ አለቃ ጎበና ዋቆ በበኩላቸው መንግስት ያስተላለፈው ሀገር የማዳን ጥሪ ከልብ እንደሚደግፉ ገልጸው አሸባሪው ቡድን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ያደገበት የውጊያ ስልቱ በመሆኑ ማንም ሊረበሽ እንደማይገባ አሳስበዋል።
የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን በሚደረገው ትግል በመሳተፍ የቡድኑን የጥፋት ሴራ ለማክሸፍ ዳግም እዘምታለሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!