3 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎችን የሰረቁ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው 3 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎችን የሰረቁ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
ወንጀሉ የተፈፀመው በየካ ክፍለ ከተማ አያት አደባባይ አካባቢ በሚገኘዉ ቻርጄር ጀኔራል ቢዝነስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ውስጥ ነው፡፡
ድርጅቱ በቁጥር አራት የሚሆኑ ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎችን የመሸጥ ፍላጎት ስለነበረው ተጠርጣሪዎቹ መኪናዎቹን እንገዛለን በማለት ወንጀሉን ከመፈፀማቸው ከአንድ ሳምንት በፊት መጥተዉ እንደተመለከቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ሀምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ድርጅቱ በመምጣት እና ለተቋሙ የጥበቃ ሰራተኞች እኛ የመረጃ እና ደህንነት አባሎች ነን ብለው በመንገር አፍነዉ ወደ ህንፃው የምድር ወለል ውስጥ ማስገባታቸው ተገልጿል።
በመቀጠልም ቆመው ከነበሩት አራት ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች መካከል 7ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የዋጋ ግምት ያላቸው 3 ሲኖትራክ መኪናዎች ይዘው መሰወራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው በኋላ ባደረገው ብርቱ ክትትል ሁለቱን ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና አንደኛውን ተሽከርካሪ በ860 ሺህ ብር የሸጡት በመሆኑ እሱንም ለማስመለስ በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ ፖሊስ ገልጿል።
ከጎዳዩ ጋር በተያያዘ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!