Fana: At a Speed of Life!

ለ9 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ቀርቧል- የውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ለሚሆኑ÷ በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በሀገር ውስጥ እንቦጭን የማጥፋት ሥራ ጨምሮ፣ የሕዳሴውን ግድብ ድርድር እንዲሁም በሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሌት አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውን የ2013 የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በሚያካሂዱበት መድረክ አብራርተዋል፡፡

በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍም በ2013 በጀት ዓመት ከክልል መንግሥታትና ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ በተከናወኑ ተግባራት በአጠቃላይ 9 ሺህ 4 መቶ 71 አዲስ የመጠጥ ውሃ ተቋማት መገንባታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በገጠር 2 ነጥብ 5 ሚሊየን እና በከተማ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በድምሩ 4 ሚሊየን ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው፡፡

በድርቅ በተደጋጋሚ በሚጠቁ አካባቢዎች 15 የባለ ብዙ መንደር መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የ23 ከተሞች የተቀናጀ የከተማ ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችና የገጠር ሳኒቴሽን በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በ2030 ለሁሉም ዜጎች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽንን ለማቅረብና የዘላቂ የልማት ግብን ለማሳካት እየተሰራም ነው ነው ተብሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ 9 ነጥብ 2 ሚሊየን ለሚሆኑ÷ በድርቅ፣ በጎርፍና በግጭት ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ለ13 ከተሞች የ769 ሚሊየን ብር የረጅም ጊዜ ብድር ስምምነት ውል መፈፀሙን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙት÷ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የውሃ ልማት ኮሚሽን፣ የውሃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል የውሃ ቢሮ ኃላፊዎችና የልማት አጋር ተወካዮች መሆናቸውን ከውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.