የዘይት ገበያን ለማረጋጋት የምግብ ዘይት ምርት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘይት ገበያን ለማረጋጋት የምግብ ዘይት ምርት ወደ ሃገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
መንግስት እየተፈጠረ ያለውን ሀገራዊ የገበያ አሻጥር ከመከላከል ጎን ለጎን መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ከውጭ በማስመጣት የህብረተሰቡን ኑሮ ለመደጎም እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ከውጭ በሚገባ ምርት ብቻ ገበያን ማረጋጋትም ሆነ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እና የሀገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ የማይቻል በመሆኑ በ2013 በጀት ዓመት ሁለት ትላልቅ የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም አሁን ላይ የተፈጠረውን ጊዜያዊ አለመረጋጋት በመጠቀም አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች መኖራቸውን ገልጿል።
በዚህም በአጭር ጊዜ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም ነው የገለፀው፡፡
እየተከሰተ ያለውን የሸቀጦች ዋጋ መጨመር ለማስተካከል ይረዳ ዘንድም 31 ሚሊየን ዶላር በመመደብ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ከ24 ሚሊየን ሊትር በላይ እና በንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አማካኝነት 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በድምሩ ከ36 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት የግዥ ስርዓቱ ተጠናቅቆ ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው ተብሏል፡፡
የዘይት ምርቱ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በፍጥነት የሚደርስበት ስርዓት ቀድሞ የተሰራ በመሆኑ የማጓጓዝ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ ለህብረተሰቡ እንደሚሰራጭ ከንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ያኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!