Fana: At a Speed of Life!

የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቆጣጠር የተጀመረው ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምሁራን አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋሉ ያሉ የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስት የጀመረውን ርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የዘርፉ ምሁራን አሳሰቡ።

ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሀሳባቸውን የሰጡት ምሁራን በአሁኑ ጊዜ የሚፈጠር የኢኮኖሚ አሻጥር ሆን ተብሎ ፖለቲካዊ ውጥረት የመፍጠርና ስርአቱን የማናጋት ግብ ያለው ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ምትኩ ከበደ ለፋና ሪፖርተር እንደነገሩት፥ የኢኮኖሚ አሻጥር ፖለቲካዊ ውጥረት መፍጠሪያ የሴራው ጉንጉን ከለውጡ በፊት ከነበሩት የኢኮኖሚ ፈላጭ ቆራጮች የሚመነጭ ነው።

የኢኮኖሚ አሻጥሩ የሴራ ባህሪ በሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ዘርፉን እንዳሻው እየከፈተና እየዘጋ የተጽዕኖ በትሩን በመንግስትና በህዝብ ላይ ለማሳረፍ የሚሞክር ነው ይሉታል።

የኢኮኖሚ አሻጥሩ ከመሰረታዊ ፍጆታ አንስቶ እጁን ያረዘመ ነው ያሉት አቶ ምትኩ ፥ የዋጋ ንረት አባባሽ ተንኮሎች ውስጥ ተሰማርቶ በኢኮኖሚ ሽፋን ፖለቲካዊ ትርፍን ኢላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ተንታኙ ዋሲሁን በላይ በሰጡት አስተያየት በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን በማድረግ ይገለጻል።

ትርፍ የማጋበስና ህዝብ የማማረር ስራ ላይ የተጠመደ ህገ ወጥ ነጋዴ ከኑሮ ውድነቱ ጀርባ የቆመ ፈተና ነው ብለውታል።

ይህን የኢኮኖሚ አሻጥር ለመቆጣጠር መንግስት ባለፉት ሳምንታት የጀመረው እርምጃ ቢዘገይም ተገቢ ውሳኔ ነው ይሉታል የኢኮኖሚ ምሁራኑ።

የዋጋ ንረቱን ከማረጋጋት እስከ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ድረስ መንግስት እጁን በማርዘም በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ምሁራኑ ባለፉት ሳምንታት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ህገ ወጦች ላይ ርምጃ የመውሰድ ጅምሮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

ኃይለየሱስ መኮንን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.