አሸባሪው የትህነግ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት ተፈጽሟል – የጥናት ውጤት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል ባካሄደው ወረራ አራት መሰረታዊ የጦር ስልቶችን እና ስትራቴጂዎችን በተጠና መልኩ በመጠቀም በርካታ የሽብር፣ ማጭበርበር፣ የዘረፋ እና የውድመት ድርጊቶችን መፈጸሙን በጉዳዩ ላይ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ቡድን በደቡብ ጎንደር ዞን ከነሐሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለ9 ቀናት ባደረገው ወረራ መጠነ ሰፊ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን በጥናት አረጋግጧል፡፡
የጥናቱ አባል እና በሙያቸው ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ እንዳብራሩት÷ በትህነግ ወረሪ ቡድን በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና የሃብት ዘረፋና ውድመት ተፈጽሟል ፡፡
አሸባሪው ቡድን በወረራው አራት መሰረታዊ የጦር ስልቶችን እና ስትራቴጂዎችን በተጠና መልኩ መጠቀሙን አቶ ቴዎድሮስ ጠቅሰዋል፡፡ ሽብር፣ ማጭበርበር፣ ዘረፋ እና ውድመት። አሸባሪው ቡድን እንደሁኔታው በቅደም ተከተል ተግባራዊ የተደረጉ የወረራ ስልቶችም ነበሩት ነው ያሉት፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚሉት÷ በከተሞች እና ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመተኮስ፣ ሰርጎ ገቦችን እና የውስጥ ተላላኪዎችን መጠቀም እና ኹከት መፍጠር የአሸባሪው ቡድን ተቀዳሚ ተግባራት ነበሩ፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በቀጣይ የተከተለው ተግባር ህብረተሰቡን የማግባባትና ማጭበርበር ነው ይላሉ አቶ ቴዎድሮስ፡፡
ቡድኑ “እኛ የምንፈልገው መንግሥትን ነው፤ እናንተን የማስተዳደር ሕጋዊ መብት የለንም፤ የጎበዝ አለቃ ምረጡ፤ የጦር መሳሪያ ያለው ብቻ ያስረክብ እና የሸሹ ንጹሃን ካሉ መልሷቸው” በማለት በነዋሪው ሕዝብ ዘንድ የማታለልና የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሟል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፥ ይህም የወረራው ሁለተኛ ክፍል እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በሦስተኛ ክፍል የሚመጣው ቡድኑ በቁጥር በርካታ እና የተደራጀ ተልዕኮ የያዘ ነው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ፥ በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድንን ያካተተ ነው ይላሉ፡፡ የሕክምና፣ የምህንድስና፣ የመካኒኮች እና የተለያዩ ዘርፎች ቡድን ቀድሞ በተጠና መልኩ ወደ ከተሞች ከገባ በኋላ በየዘርፉ ተቋማትን፣ ፋብሪካዎችንና የንግድ ድርጅቶችን እንደሚቆጣጠር በጥናቱ ታይቷል ነው ያሉት።
በዚህ መንገድ በዘረፋ ቡድኑ የሕክምና፣ የምህንድስና እና የፋብሪካ ማሽኖች በጥንቃቄ ተነቅለው መዘረፋቸው በጥናቱ መረጋገጡን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በየግለሰቦች ቤት ፍተሻ እና ብርበራ በማካሄድ የግለሰቦች ሃብትና ንብረት፣ ጌጣጌጥ እና ሙዳየ ምጽዋት ሳይቀር ተሰርቀዋል ተብሏል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ እንዳብራሩት አውዳሚ ወይም የአካባቢው ማኅበረሰብ “ጀሌ” በሚል የሚጠራቸው ገጀራ እና መሰል ስለታም መሳሪያዎችን የያዘ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቡድን ገብቶ ከዘረፋ የተረፉትን እና መንቀሳቀስ የማይችሉትን ሁሉ አውድሟል፡፡
የትምህርት እና የጤና ተቋማት የዚህ ቡድን ሰለባ ሆነዋል፡፡
የሕክምና እና የትምህርት መረጃዎች ተቃጥለዋል፤ ኮምፒውተሮች እና ሸልፎች ተሰባብረዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን የተወሰኑ አካባቢዎች ለዘጠኝ ቀናት በዘለቀው የአሸባሪው ቡድን ወረራ መጠነ ሰፊ ዘረፋ ተፈጽሟል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ፥ በሌሎች አካባቢዎች ሊኖር የሚችለውን ጉዳት መገመት አዳጋች አይደለም ብለዋል፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው “አሸባሪው ቡድን በወረራው የተደራጀ፣ በባለሙያዎቹ የተደገፈ እና ከፍተኛ ሃብት ዘረፋ አካሂዷል” ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፡፡
በሁሉም አካባቢዎች የአሸባሪ ቡድኑን የወንጀል ተግባራት በዝርዝር በማጥናት የፈጸመውን የግድያ፣ የዘራፊነት ደረጃ፣ ዓይነትና መጠን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር በዝርዝር ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያው መጠቆማቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!