የደነባ ዋሻ መስራችና ባለቤት አቶ ገመዳ ዋይሶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ገመዳ ዋይሶ፣ ሰንበቴና አሚና የሰው ሰራሽ ዋሻና የመዝናኛ ሥፍራ በተለምዶ ደነባ ዋሻ መስራችና ባለቤት አቶ ገመዳ ዋይሶ በ65 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አቶ ገመዳ ዋይሶ ከ 1971 እስከ 1992 ዓ.ም ለ21 ዓመታት ዋሻውን በመቆፈር የቆዩ ሲሆን÷ ከ1992 ዓ.ም በኋላም ለህዝብ ክፍት በማድረግ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አድርገዋል።
አቶ ገመዳ የአካባቢው የውሃ ችግርን ተከትሎ ውሃ ለማቆር በሚል ጉድጓድ ከቆፈሩ በኋላ በተደጋጋሚ በሥፍራው ዋሻ እንዲሰሩ በራዕይ በማየታቸው የዋሻ ቁፋሮውን ስለመቀጠላቸው ከሻሸመኔ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ቁፋሯቸውንም ጥቂት ቦታ ለግብርና በማስቀረት በ3 ሺህ ካሬ የእርሻ መሬታቸው ላይ በመቀጠል አሁን ላይ 36 ክፍሎችና 12 መግቢያና መውጫ በሮች ያሉት ዋሻ መስራት ችለዋል።
ዋሻው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ጎብኚዎች የሚጎበኘ ሲሆን÷ አቶ ገመዳ ዋይሶ ቤተሰቦቻቸውን ከዛው በሚገኝ ገቢ እንደሚያስተዳድሩ ተገልጿል፡፡
ይህንንም አጠናክረው ለማስቀጠል ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ገመዳ ዋይሶ ፣ ሰንበቴና አሚና የሰውሰራሽ ዋሻና የመዝናኛ ሥፍራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል ስያሜ ፍቃድ በማውጣት የመዝናኛ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
አቶ ገመዳ ዋይሶ ከአባታቸው አቶ ዋይሶ ባነታ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ሳፋዬ በሪሶ በ1948 ዓ.ም ቡልቻና ደነባ ቀበሌ ተወልደው ባደረባቸው ህመም መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤አቶ ገመዳ የ12 ልጆች አባት ነበሩ፡፡
የቀብር ስነ ሥርዓታቸውም ቤተሰባቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት በሻሸመኔ ወረዳ ቡልቻና ደነባ ተከናውኗል።
ፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬትም በህልፈታቸው የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል።
በታምራት ቢሻዉና ለማ ተስፋዬ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!