የተመሰረተዉ መንግስት ሰላምና ኢኮኖሚዉ ላይ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣መስከረም 25፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን የተመሰረተዉ መንግስት ሰላምና ኢኮኖሚዉ ላይ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የፖለቲካ አመራሮች አስተያየት ሰጡ፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በመንግስት መስረታ እና በዓለ ሲመት ላይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መንግስት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ወቅት ነዉ ያሉት የራዕይ ተጋሩ ኢትዮጵያዊያን ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሊላይ ኃ/ማርያም÷ህዝቡ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመራዉን ድርጅት መርጧል ቀጣይም መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ህጋዊ በሆነ መንገድ መጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጣይ አምስት አመታት በኢኮኖሚ በልጽጋ፣በአንድነት ተባብረን፣ተፋቅረን የምንኖርባት ታላቋን ኢትዮጵያ እንደምናይ እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አቶ ሰይፈስላሴ አያሌዉ÷ለቀጣይ አምስት አመታት ኢትዮጵያን የሚመራዉ መንግስት ለየት ያለ ነገር ማምጣት መቻል አለበት ነው ያሉት፡፡
ባለፉት 30 አመታት ኢትዮጵያ የሄደችበት መንገድ ብዙ የተማርንበት፣ኢትዮጵያ የተጎዳችበት፣ህዝቦቿ የተጎዱበት፣የተከፋፈልንበት ጊዜ ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነት ላይ ጠንክሮ መስራት የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ሰይፈስላሴ አያሌው፥ መሪዉና ተመሪዉ የየራሳቸዉ ሚና እናዳላቸዉ እና ሁላችንም የየራሳችንን ሀላፊነት እንደ ዜጋ መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
አሁን የተመሰረተዉ መንግስት ሰላምና ኢኮኖሚዉ ላይ በቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የገለጹት የበዓለ ሲመቱ ተሳታፊ አቶ ቢኒያም አበበ ናቸዉ፡፡ ህዝቡም ከማማረር ይልቅ መንግስትን ደግፎ ወደ ስራ መግባት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዷለም አድማሴ በበኩላቸዉ÷አዲስ ምዕራፍ፣አዲስ መንገድ ነዉ የምንጀምረዉ ኢትዮጵያን አንድ ከፍታ ይዘን የምንሄድበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል፡፡
እኔ በምመራበት ተቋም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን በተቻለ ጥረት ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል እንሰራለንም ነዉ ያሉት፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!