የማዕከላዊ አየር ምድብ በስራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የሰራዊቱ አባላት የማእረግ ሹመት ሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአየር ኃይል ማዕከላዊ አየር ምድብ በስራ አፈፃፀማቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ እና የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ የሠራዊት አባላት የማዕረግ ሹመት ሰጠ፡፡
በሐረር ሜዳ በተከናወነው ስነስርዓት ላይ በመገኘት የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለሎጀስቲክ ብርጋዴር ጄነራል ነገራ ሌሊሳ ለማዕረግተኞች አልብሰዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም ሪፎርሙ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ አየር ኃይሉ በሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል::
የህወሐት አሸባሪ ቡድን የፈፀመውን ወረራ በመቀልበስ ረገድ አየር ኃይላችን ከፍተኛ ጀግንነት እየፈፀመ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
ለዘመቻው ስኬታማነት ማዕከላዊ አየር ምድብ ያበረከተው እና እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የማዕከላዊ አየር ምድብ አዛዥ ኮለኔል ወንዱ ኪዳ በበኩላቸው÷ አየር ምድቡ የህወሓት አሸባሪ ቡድን በሰሜን ዕዝ ብሎም በአማራ እና በአፋር ክልል የፈፀመውን ወረራ በመቀልበስ አኩሪ ድል አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
የምድቡ ፈጣንና ውጤታማ የግዳጅ አፈፃፀም የሽብር ቡድኑ ሙሉ በሙሉ እስኪደመሰስ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።
የምድቡ ምክትል አዛዥ ለሰው ኃብት ልማት ኮለኔል ወርቁ ፈረደ የዛሬ ተሿሚዎች ሁሉንም መመዘኛ አሟልተው የተገኙ መሆኑን ገልፀዋል::
በስነ-ስርዓቱ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሿሚዎች በሰጡት አስተያየት የማዕረግ እድገቱ ለበለጠ ስኬትና ጀብድ የሚያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የተጀመረውን ዘመቻ አጠናክረው በመቀጠል አገራቸውንና ህዝባቸውን ከጥፋት ኃይል ለመታደግ ዝግጁ እንደሆኑም አረጋግጠዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!