የሱዳን ኤሌክትሪክ ኩባንያ ልዑክ አዲስ አበባ ገባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን ኤሌክትሪክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቴክኒክ አማካሪ የተመራ የልዑክ ቡድን በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በቀጣይ ስለሚኖረው የኃይል ትስስር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኃላፊዎች ጋር ለመደራደር አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
በአህመድ አደም ኡመር የተመራዉ ልዑኩ÷ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የስትራቴጂና ኢንቨስትመንት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ተሾመ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ የገባው በሁለቱ ሃገራት መካከል የኃይል ትስስሩን ለማጠናከር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ላይ ድርድር ለማድረግ መሆኑን አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች በካርቱም በመገኘት ከኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ጋር መደራደራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚካሄደው ድርድር ከዚህ በፊት በነበሩ ድርድሮች የተነሱ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና በቀጣይ ስለሚኖረው የአሰራር ሁኔታ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነውም ብለዋል፡፡
ድርድሩ የሱዳን የኤሌክትሪክ ኩባንያ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ 1 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ባቀረበው ጥያቄ ላይ እንዲሁም ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ መከናወን ባለበት የመስመር ዝርጋታ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታዎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ እንደሚሆንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ድርድሩ ከጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት እንደሚካሄድም ነው የተገለፀው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሱዳን 230 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ ትገኛለች፡፡
ከሱዳን በተጨማሪም ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ላይ የምትገኝ ሲሆን÷ ለኬንያ የአሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ እቅድ መያዙም ተጠቁሟል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ፣ ከሶማሊያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኤርትራ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ መሆኗን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!!