አካታች የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋቱ ሀገሪቱን ከችግር ያድናል – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) አካታች የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋቱ በሁሉም ዘርፍ የዜጎችን ተሳትፎ በማጎልበት ሀገሪቱ ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት÷ አዲሱ የመንግስት አደረጃጀት በተለይ የየራሳቸው ርዕዮት ዓለም ያላቸውን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ መሆኑ ሀገርን ያስቀደመና ለትክክለኛ ዴሞክራሲ መጎልበት መሰረት የጣለ ነው።
የተለያዩ ፓርቲዎችን በሀገራዊ ጉዳይ ወሳኝ አካል በማድረግ ማካተት መቻሉ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት በጎ ተግባር መሆኑን የተናገሩት ምሁራኑ÷ መንግስት ሀገሪቱን ከገጠማት ውስብስብ ችግር በማላቀቅ የዜጎችን አንድነትና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር የሆኑት አቶ ኡመር መሐመድ ኑር÷ ከዚህ ቀደም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር ተቀናጅተው በሀገር ግንባታ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት ዕድል አልነበራቸዉም ነዉ ያሉት፡፡
በዚህም ለሀገር ይበጃል ብለው የሚያስቡትን እሳቤና ፕሮግራም በመተግበር ተሳታፊ መሆን እንዳልቻሉ አስረድተዋል።
አሁን በተመሰረተው መንግስት ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የነበረውን ችግር ይፈታል ብለው እንደሚያምኑም ነው ያመላከቱት፡፡
በተለይ አካታች የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋቱ በሁሉም ዘርፍ የዜጎችን ተሳትፎ በማጎልበት ሀገሪቱ ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትወጣ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ አቶ ሌንጮ ሳሙኤል ናቸው።
አዲሱ መንግስት ዴሞክራሲን ከማዳበር ባለፈ ሀገሪቱን ከገጠማት ወቅታዊ ችግር በማውጣት ጠንከራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል።
ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ ለማሻገር መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ህዝቡ ከጎኑ በመሆን ማገዝ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ዶክተር መሐመድ ጀማል በበኩላቸው÷ መንግስት የመረጠውን ሕዝብ የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን የመመለስና የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሥራዎች የሀገሪቱን ጥቅም አሳልፎ በማይሰጥ መልኩ መፈጸም የአዲሱ መንግስት ቀጣይ የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ሕዝቡ በሚደግፈው ልክ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከምንጊዜውም በላይ መስራት እንዳለበት ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡
ህዝቡም በራሱ ተወካዮች የተመሰረተውን መንግስት በመደገፍ ለሀገሩ ሰላምና ልማት መረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!