ህወሓት እና የጋላቢዎቹ ሴራ የሚከሽፍበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል- አቶ እርስቱ ይርዳው
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚጠላትን አገር በመሪነት ስም ሲበዘብዝ የከረመው አሸባሪው ቡድን ጥቅሜ ቀረብኝ በሚል ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሴራ ጋብቻ ፈፅሞ ያጠባ ጡቷን ደጋግሞ እየነከሰ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ገለፁ።
በታሪክ አጋጣሚ አገር የማስቀጠል ሀላፊነት የተሸከመው ብልፅግና ፓርቲም የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብሮ ተከብራ የኖረችውን አገር ክብሯ ሳይሸራረፍ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቆራጥነት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አገር በማዳን ዘመቻው ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከግንባር እስከ ደጀንነት በመሳተፍ፥ በቅርቡ አሸባሪው ቡድን እና ጋላቢዎቹ የኢትዮጵያን አይደፈሬነት እንዲገነዘቡ ይደረጋል ብለዋል።
ማንኛውም ስምና ዝና ከአገር ህልውና እንደማይበልጥ የተናገሩት አቶ እርስቱ በየትኛውም ሀላፊነት፣ አካባቢና ሁኔታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የአገርን ህልውና ለማስጠበቅ በምናደርገው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ለጊዜው በመተው ለእናት አገራቸው በአንድ በመቆማቸው የአሸባሪውን እና የጋላቢዎቹን ሴራ የምናከሽፍበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ሲሉ ገልፀዋል።
በሞሊቶ ኤልያስ