በዩኔስኮ ከተመዘገበ 4 ዓመታትን ያስቆጠረው የማጃንግ የተፈጥሮ ደን እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል- የጋምቤላ ክልል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥብቅ የተፈጥሮ ደንነት ዩኔስኮ የመዘገበው የማጃንግ የተፈጥሮ ደን በአካባቢው ማህበረሰብና በባለድርሻ አካላት እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ተናገሩ፡፡
የተፈጥሮ ደኑ በዩኔስኮ የተመዘገበበት 4ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በሜጢ ከተማ ተከብሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ቴንኩዌይ ጆክ፥ ደኑ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙና ተጠብቀው ከቆዩ ሀብቶች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፥ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ከፍኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የደን ሀብቱ በዓለም እውቅና አግኝቶ ከተመዘገበ አራት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ጠቅሰው፥ ይህም በሀገሪቱ ለተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀጣይነት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የዞኑ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የደን ሀብቱን ይበልጥ በመጠበቅ ልማቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡
የማጃንግ ጥብቅ ደን የቆዳ ስፋቱ 225 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ሲሆን፥ 43 ሺህ 882 ሔክታር የሚሸፍን ጥብቅ ደን ነው፡፡
በውስጡም 550 የሚደርሱ የእጽዋት፣ ከ180 በላይ የአዕዋፍ፣ 33 የአጥቢ እንስሳትና 20 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኙበታል።
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!