በኦሮሚያ ክልል የሴቶችና ሕፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሴቶችና ሕፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል አለ የክልሉ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ።
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ መብራት ባጫ እንዳሉት ÷ መንግሥት የሴቶችና ሕፃናትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
በክልሉ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ችግሮች ከመሠረቱ ለመፍታት ሰፊ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም ሴቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲችሉና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሴቶችን በማደራጀትና በማጠናከር ረገድ በተከናወነው ሥራ 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ሴቶችን ማደራጀት ተችሏል ነው ያሉት።
የሕፃናትን ተጠቃሚነትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሕፃናት ፓርላማን በማቋቋም እንዲሁም 1 ሺህ 980 የሕፃናት ማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ረገድ ሰፊና አወንታዊ ሥራ መከናወኑን ሃላፊዋ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ቢሮው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውሰው ÷ እስካሁን 156 ሺህ የሚሆኑ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በመገንባት የማሕበረሰቡን ችግር የፈታ ትልቅ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ቢሮው “በሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበቻ እና የጾታ እኩልነት ፖሊሲ“ ላይ በየደረጃው ለሚገኙ መዋቅሮቹ የአቅም ግንባታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።