Fana: At a Speed of Life!

በጎንደር ታላቅ አውደ ርዕይ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተገኙበት ታላቅ አውደ ርዕይ ዛሬ በጎንደር በራስ ግምብ ተከፍቷል፡፡
በአውደ ርዕዩ ከ150 ዓመታት በላይ በስደት የቆየው የአፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ እና ሌሎች 21 ቅርሶች ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ሆነዋል፡፡
ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጎንደር ከተማ እየገቡ ነው፡፡ ጎንደርም እንግዶቿን በኢትዮጵያዊ ወግ እና ባህል እየተቀበለች ነው፡፡
ከጥምቀት በዓል ጎን ለጎንም ሲምፖዚየም፣ አውደ ርዕይ እና ባዛር፣ የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የንጉሥ እና የምሥጋና የእራት ግብዣ መርሀ ግብርም እየተከናወኑ ናቸው፡፡
የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሥራች የነበሩት አፄ ቴዎድሮስ ሹሩባ ለሕዝብ ጉብኝት ክፍት መሆኑ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመመስረት የአንድነት ተምሳሌት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል በመልዕክታቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም በአውደ ርዕዩ በመታደም የከፍታችንን ደረጃ እና የማንነታችንን ምሰሶ የት እንደነበር ሊመረምሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
በሀገር ውስጥ በረራ ታሪክ ክብረ ወሰን የሆነ መጠን በጎንደር ተመዝግቧል ያሉት ዶክተር ይልቃል፥ ይህም አካባቢው ሰላም፣ የተረጋጋ እና ለእንግዶች ምቹ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
እንግዶችም በቆይታቸው ያለምንም ስጋት በዓሉን እና የእረፍት ጊዜያቸውን በጎንደር ያሳልፋሉ ብለዋል፡፡
ዶክተር ይልቃል የጎንደር ከተማ ሕዝብም በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ የቆየው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያንሰራራ የሰላሙ ዘብ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
“ጎንደር የሰላም፣ የታሪክ እና የእምነት ከተማ ናትና እንግዶች በቆይታችሁ በብዙው አትርፋችሁ ትመለሳላችሁ” ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
ጥምቀትን ብቻ ሳይሆን ከጥምቀት በኋላ ባሉ ቀናትም እልፍ የሆኑትን የታሪክ፣ የእምነት እና የማንነት አሻራዎች በወጉ እንዲጎበኙ ጋብዘዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆንላቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና እንግዶች መታደማቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
+4
0
People reached
0
Engagements
Boost post
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.