የመጀመሪያው የሶማሌ ክልል የሸበሌ ባንክ የምስረታ ሥነ ስርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የሶማሌ ክልል የሸበሌ ባንክ የምስረታ ሥነ ስርዓት በጅግጅጋ ከተማ ተካሄደ፡፡
የሶማሌ ክልል አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም የሆነው “ሄሎው ካሽ ” በ2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባገኘው እውቅና መሰረት ወደ ሸበሌ ባንክነት ማደግ እንደቻለ ተገልጿል፡፡
ተቋሙ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የሀብት መጠን ማስመዝገቡም ተመላክቷል፡፡
በባንኩ ምስረታ መርሀ ግብር ላይ የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ የባንኩ የቦርድ አመራር ሰብሳቢ አቶ ሀሰን መሐመድ እና ሌሎች የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ነው የተባለው።
ባንኩ ከመመስረቱ በፊት የሶማሌ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ሆኖ መቆየቱን የገለጹት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ÷ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በኑሮ እራሳቸውን እንዲችሉና የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በተለያዩ ዘርፎች የብድር አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ባንኩ በክልሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ከመቅረፍ አንፃር ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችልም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል፡፡
ወደ ሸበሌ ባንክነት ያደገው የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም እንደ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህብረተሰብ በኢኮኖሚ እየደገፈ መሆኑን የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሀሰን መሀመድ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ በሚሰጠው የሸሪዓ ባንክ አገልግሎት ግቡ “ማህበረሰባዊ አገልግሎቱን ቀላል፣ ግልፅና ቀልጣፋ ማድረግ ነው” ብለዋል።
በባንኩ ምስረታ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት አምባሳደር መሀሙድ ድሪር በበኩላቸው፥ የባንኩ መመስረት ለክልሉ ህብረተሰብና ለሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወተው ሚና ትልቅ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አምባሳደር መሀመድ ድሪር ናቸው፡፡
ለባንኩ ምስረታ መሳካት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና እውቅናና የሽልማት መበርከቱን ከሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!