ንግድ ባንክ ያስገነባውን አዲስ የዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ዛሬ ያስመርቃል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ይመረቃል፡፡
አዲሱ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ከመሬት በላይ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ፥ ባለ 53 ወለል ነው።
በውስጡም የቢሮ አገልግሎት ከሚሰጡ ክፍሎች በተጨማሪ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ ሙዚየም እና ሲኒማ ቤትን ያካተተ ሲሆን፥ እስከ 1 ሺህ 500 መኪናዎችን መያዝ የሚችል ማቆሚያም አለው።
5 አመት ከ11 ወር የወሰደው ግንባታው 303 ሚሊየን 500 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
በኢትዮጵያ ከ117 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የባንክ ሥራ ታሪክ ውስጥ ዘለቄታ ያለው መሠረት ጥሎ ያለፈው በ1935 ዓ.ም በ1 ሚሊየን ማርያትሬዛ ካፒታል የተመሠረተው የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ የብሄራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን ሚና ሲወጣ ቆይቶም በ1955 ዓ.ም ለሁለት ተከፍሎ የኢትዮጵያን ገንዘብ ቁጥጥርና የማሳተም ኃላፊነት ለብሄራዊ ባንክ ፤ የንግድ ሥራ ዘርፉ ደግሞ ለአሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሰጠቱን ባንኩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ከታሪክ መዝገብ አጣቅሶ ያስመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ለህብረተሰቡ የባንክ አገልግሎትን በማዳረስ፣ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ በሀገራችን የሚከናወኑ በርካታ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ዛሬም ባንኩ የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንና የአዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ምረቃ ስነስርዓቱን በድምቀት እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!