Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ሩሲያን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚወስደው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ የድርጊት መርሐ ግብር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ከጊሲ ሮሳት ኩባንያ ጋር የተደረሰው የድርጊት መርሐ ግብር ስምምነት የኢትዮ-ሩሲያን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ይወስደዋል አሉ።

በሩሲያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ከተወያዩ በኋላ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።

በኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን አስታውሰው፤ ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችል የድርጊት መርሐ ግብር ከጂሲ ሮሳት ጋር ስምምነት ተደርጓል ነው ያሉት።

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሞስኮ ባደረጉት ጉብኝት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መወያየታቸውን ያስታወሱት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፤ ምክክሩ የሀገራቱን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያጠናከረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በሀገራቱ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውን ገልጸው፤ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በሩሲያ የነበራቸው የሥራ ጉብኝት ግንኙነቱን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ሁለቱ ሀገራት ሌላ የመወያያ አጀንዳ እንዲኖራቸው ማድረጉን አንስተው፤ በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.