የአልጄሪያ – ኢትዮጵያ ፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ተመሠረተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአልጄሪያ ብሔራዊ የሕዝብ ሸንጎ የኢትዮጵያና የአልጄሪያን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የአልጄሪያ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን በዛሬው ዕለት ተመስርቷል።
የአልጄሪያ-ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን ምሥረታን ምክንያት በማድረግ በፓርላማው የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ የፓርላማው የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሃኒ መሐመድ ÷ኢትዮጵያና አልጄሪያ በፖለቲካ መስክ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ግንኙነትም በፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲያዊ በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቁት።
የአልጄሪያ ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን ሊቀመንበር ሆነው የተሠየሙት መሐመድ ሬዳ ቤንአልጊ በበኩላቸው÷ እርሳቸውም ሆኑ የቡድኑ አባላት ለኢትዮጵያና አልጄሪያ ሁለንተናዊ ግንኙነት መጎልበት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ÷በአልጄሪያ ፓርላማ የአልጄሪያ – ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን መመሥረት የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነቱ መጠናከርም በሁለቱ ህዝቦች መካከል ከፖለቲካውም ባሻገር የህዝብ ለህዝብ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር አመቺ ዕድል እንደሚፈጥር መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአልጄሪያ ብሔራዊ ሕዝባዊ ሸንጎ 407 የፓርላማ አባላት ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።