Fana: At a Speed of Life!

በፋና ላምሮት የድምፃውያን ውድድር ያለምወርቅ ጀምበሩ አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ በተካሄደው የፋና ላምሮት ምዕራፍ 10 የፍጻሜ ውድድር ድምፃዊት ያለምወርቅ ጀምበሩ አሸነፈች፡፡
 
በውድድሩ ምዕራፍ የመጨረሻ ዙር የቀረቡት ድምፃውያን ዳንኤል አዱኛ ፣ ደሳለኝ አበበ፣ያለምወርቅ ጀምበሩ እና ገረመው ገብረፃዲቅ በሦስት ዙር የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ለዳኞችና ለተመልካቾች በቀጥታ አቅርበዋል፡፡
 
ዳኞችም በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት የየራሳቸውን ነጥብ የሰጡ ሲሆን፥ ያለምወርቅ ጀምበሩ የተጋባዥ እንግዳው የድምፃዊ ተሾመ አሰግድ ነጥብና የተመልካቾችን ነጥብ በማካተት 104 ሺህ 263 ነጥብ በማግኘት የምዕራፉ የማጠቃለያ ውድድር አሸናፊ በመሆን የ200 ሺህ ብር አሸናፊ ሆናለች፡፡
 
ዳንኤል አዱኛ 99 ሺህ 247 ነጥብ በማምጣት ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የ150 ሺህ ብር አሸናፊ መሆን ችሏል፡፡
 
ደሳለኝ አበበ እና ገረመው ገብረፃዲቅ 3ኛ እና 4ኛ በመውጣት በቅደም ተከተል የ100 ሺህ ብር እና የ50 ሺህ ብር አሸናፊ ሆነዋል፡፡
 
ለአሸናፊ ድምፃውያኑ ሽልማታቸውን የሰጡት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ባደረጉት ንግግር ÷ “ፋና ላምሮት ትውልድ የሚቀረፅበት፣ ዕድል ያላገኙ ወጣት ድምፃውያን ዕድል የሚያገኙበት ፣ ጥበብ ጥበበኞችን ከፍ የምታደርግበት፣ ሙያና ሙያተኛ የሚገናኝበት መድረክ ነው” ብለዋል፡፡
 
ፋና ላምሮት ዳኞች፣ ተወዳዳሪዎች፣ የፕሮግራሙ ተጋባዥ እንግዶችን በተለይም የፋና አድማጭ ተመልካቾችና ደንበኞች ለዝግጅቱ መሳካት ላደረጉት አስተዋፅኦም አመስግነዋል።
 
ዕድሉን ያላገኙ እና ዕድሉን ለማግኘት እየሞከሩ ያሉ ከብዙ ቦታዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች፥በአጠቃላይ ፋና ላምሮት ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የጥበብ ቤተሰቦች በርካቶች መሆናቸውን ነው አቶ አድማሱ የገለጹት፡፡
 
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፥ ፋና ለጥበብ እጅግ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጥ፥ የጥበበኞች ቤት ሲሆን፥ ጥበበኞችም የፋና ቤተሰቦች ናቸው፡፡
 
የፋና ላምሮት መድረክ ÷ ትናንት መልካም የሠሩትን እያመሰገንን፥ ዛሬን ለነገ ተዘጋጅተን የተሻለ ለማድረግ የምንጥርበት ነውም ብለዋል፡፡
 
አቶ አድማሱ አክለውም፥ “ሁሌ እንደምንለው ጥበብ ክብር ትፈልጋለች፤ አክባሪን ትፈልጋለች፤ ማዳመጥን ትፈልጋለች፤ ያደመጡትን መተግበርንም ትፈልጋለች” ነው ያሉት፡፡
 
ውድድሩ ዳኞችና ተመልካቾች ለጥበብ ያላቸውን ከፍታና እጅግ የላቀ ሥነ ምግባር ያሳዩበት መሆኑን ያወሱት አቶ አድማሱ፥ በመርሐ ግብሩ ላይ ልዩ ተሸላሚ የሆነውን ጥበበኛ ብላቴና ሳሙኤል ጋቶን የ40 ሺህ ብር ሸልማት ሰጥተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.