ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው ተሾሙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ሹመቱ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች የምትገኘውን የላቀ ሚና እውቅና ለመስጠት ነው።
በሹመት ደብዳቤው ላይ እንደተጠቀሰው÷ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶር) ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ያደረጉት አመራር ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ለአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነትና ለአሳታፊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል በማስቻል ረገድ ትልቅ እገዛ አድርጓል።
ስልታዊ በሆነ መልኩ የቴክኖሎጂ ነጻነትን እና ዐቅምን ለመገንባት የሚያደርጉት ተከታታይ ቅስቀሳ፣ አህጉሩ በኃላፊነትና በፍትሐዊነት በታጀበ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተመላክቷል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አመራር ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፎች ያስመዘገበችው እድገት ከፍተኛ አፈጻጸም ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የኢ መንግሥት (e-government) አገልግሎቶችን ሥራ ላይ ማዋል፣ በፈጠራ ሥነ ምህዳር ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትን ማቋቋም እንዲሁም ሀገራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስትራቴጂ መንደፍ ለለውጡ ጠንካራ መሰረት የጣሉ ተግባራት ናቸው።
በተጨማሪም ራሱን የቻለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የታቀደው ዕቅድ ምርምርን፣ የክህሎት ልማትንና አህጉራዊ ትብብርን ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ መገለጹን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡